በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ አባላትን ያሳተፈ አጠቃላይ ስብሰባ ተካሄደ::
*** *** *****
(ኮትዩ፣ መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም) በውይይቱ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተሾመ ነቃጥበብ፣ ተሰብሳቢዎችን እንኳን ለ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አደረሳችሁ በማለት፣ የውይይት መድረኩ የዓመቱ የአካዳሚክ ሥራ መጀመሩን ለማብሰር፣ በባለፈው ዓመት የታዩትን ውጤቶች በመፈተሽ ለ2019 ዓ.ም የተሻለ ተስፋና ተነሳሽነትን የምንሰንቅበት ነው ብለዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲያችን የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሆኖ በመመረጡ ዕድለኛ ነው ያሉት ፕሬዘዳንቱ፣ ከዚህ አንጻር ባለፈው ዓመት የተከናወኑት ዋና ዋና የሪፎርም፣ የአወቃቀር እና የአሠራር ተግባራት ዩኒቨርሲቲውን ወደ ስፔሻላይዝድ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና ወደ ስፔሻላይዝድ ኦቶኖመስ ዩኒቨርሲቲ የሚወስዱ መሆናቸውን፤ በዚህ ሂደትም የተዘጋጁት ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ የሴኔት ሌጂስሌሽን፣ የዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ ደንብ፣ የአካዳሚክ ሪፎርም፣ የደብል ሜጀር፣ የግንባታና መሰል በርካታ ስኬታማ ሥራዎች መሠራታቸውን፣ በ2019 የትምህርት ዘመንም እነዚህን ተግባራት አጠናክሮና አሻሽሎ የማስቀጠል ተግባራት እንደሚከናወኑም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የስትራቴጂክ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስናቀ ጉዲሳ የ2018 ዓ.ም ቁልፍ የውጤት አመላካቾችን (KPIs) ሪፖርት እና የ2019 ዓ.ም ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በተፈረመው መሠረት በተመረጡ አምስት የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውን፣ ፈጠራን እና አዳዲስ ሙከራዎችን በመሞከር፣ በቀጣይም አሰራሮቻችንን ቁልፍ የውጤት አመላካቾች (KPIs) አካል በማድረግ አፈጻጸሙን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር አለባቸው ኬሚሶ፣ የምርምርና የማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ቴዎድሮስ ሙሉጌታ፣ የአስተዳደር እና ልማት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር ሽመልስ ዘውዴ ትኩረት ተሰጥቶ በተሠራባቸው የአካዳሚክ፣ የምርምር፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የአሠራር ለውጦች ላይ የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ፣ እንዲሁም በበጀት ዓመቱ ምን ይጠበቃል፣ ምን ምንስ ይከናወናል በሚሉ ጉዳዮች ገለጻ አድርገው ውይይት ተካሄዷል፡፡
በውይይቱም፣ የቀረቡት የሪፎርም እና የግንባታ ሥራዎች የዩኒቨርሲቲውን ለውጥ የሚያሳዩ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የኦንላይን ኮርሶችን፣ ያልፀደቁ የትምህርት ፕሮግራሞችን የማየት፣ የትምህርት ጥራት ከማምጣት እንዲሁም የመምህሩን የቤት ችግሮች በፍጥነት ከመፍታት ጎን ለጎን በቀጣይ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተነሳሽነትን በመጨመር ሥራ መሥራትና የተሻለ ውጤት ማስማዝገብ እንደሚያስፈልግም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
– የህዝብ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት
