(ኮትዩ ጥቅምት18 ቀን 2019 ዓ.ም) የስልጠናው መርሐግብር በተጀመረበት ወቅት የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች አካትቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፋሲካ በላይ፣ የስልጠናው ዓላማ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ከቤተሰብ ተለይተው ለመጀመሪያ ጊዜ የዩኒቨርሲቲን ህይወት ሲቀላቀሉ ያለውን የሽግግር ሂደት ቀላልና ስኬታማ ማድረግ መሆኑን ገልፀው፣ ስልጠናው አዲስም ሆነ ነባር ለሆኑ ሴት ተማሪዎች አስፈላጊውን የህይወት ክህሎት ዕውቀት በመጨበጥ ራሳቸውን ከጉዳት ተጋላጭነት በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡
የህይወት ክህሎት ሥልጠናውን የሰጡት መምህርት ወይንሸት ለገሰ ሁሉም ተማሪዎች ከተለያየ ቦታ ከመምጣታቸው አንጻር የተለያየ ፍላጎት፣ ማንነትና አስተሳሰብ እንደሚኖራቸው ጠቅሰው፣ ይህንን ልዩነት አቻችሎ፣ አክብሮና ተቀብሎ የመኖርን ክህሎት ማዳበር እንደ ግለሰብ ከራስ ጋር፣ ከጓደኞች፣ ከመምህራንም ሆነ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጤናማ፣ የትምህርት ዘመን ቆይታቸውንም ውጤታማ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡
ራስን ከጉዳት ተጋላጭነት መከላከል ስልጠናን የሰጡት መምህርት ምኞት ጌታቸው በበኩላቸው፣ ሴት ተማሪዎች ከዓላማቸው ሊያሰናክላቸውና ጉዳት ላይ ሊጥላቸው ከሚችሉ ማንኛውም አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ራሳቸውንም ሆነ ጓደኞቻቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት፣ ጥቃትም ከደረሰ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም በሴቶች ጉዳይ ላይ ከዩኒቨርስቲው ጋር በትብብር ከሚሰራው ኤላ ሴንተር ተወክለው የመጡት ወ/ሮ ኃይማኖት፣ በቀረቡት የስልጠና ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ሙያዊ ማብራሪያና የህይወት ልምዳቸውን ለሰልጣኞቹ አካፍለዋል፡፡
– የህዝብ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት
